(የማይፈነድቁ አበቦች)
ህፃናት በብርሀን ይመሰላሉ። በዚያም ለትውልድ ያበራሉ ደስታንም ይዘው ይመጣሉ። ልክ እንደ ጠዋት ጮራ! ይህን ተስፋ ይዘው ለዓለም ሲፈነጥቁ ከተፈጥሮ ጋር ሁሉም ግብግብ ይገጥማሉ።
ዛሬ በዚህ አጭር ፅሁፍ ከብዙው የተፈጥሮ ትግል አንደኛውን ደግሞም አስከፊውን በማንሳት ትንሽ መረጃ ለማቀበል እንሞክራለን።
በተቻላችሁ መጠን ልባችሁን ሰጥታችሁ እስከ መጨረሻዋ አራት ነጥብ ድረስ ተከተሉን።
ይህን የምንለው ያለምክንያት አይደለም። እኛም ፣ አንተም ፣ አንቺም ፣ እናንተም ፣ ሁላችንም በምናደርገው ቀላል አስተዋፅኦ ያጨለጨለውን ብርሀን ፈክቶ ማየት ስለሚያስችለን ነው።
በህክምናው ዘርፍ የብዙ ህፃናትን ተስፋ የሚያጨልሙ ብዙ ችግሮች ይዘረዘራሉ። ህፃናት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ችግር ይገጥማቸዋል። የጉዳት ደረጃውም ለይቶ የሰውነት ክፍል ከማጥቃት እስከ ህይወት ማሳጣት ይደርሳል።
በሀገራችን ብሎም ሌሎች መሰል ታዳጊ ሀገሮች ላይ በመከሰት ከቀላልና የተለመደ ዓይነት ችግር እስከ ህይወት መጥፋት ደረጃ ስለሚያደርሰው የራሁማቲክ የልብ ህመም (Rheumatic heart disease) በጥቂት እንመልከት።
የራሁማቲክ የልብ ህመም በብዛት በመነሻነት የሚያጠቃው እድሜያቸው ከ 4 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ህፃናትን ሲሆን ችግሩ ከተከሰተ በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የራሁማቲክ የልብ ህመም ዕድሜያቸው ከ 4 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ላይም ሊገኝ ችሏል።
የራሁማቲክ የልብ ህመምን በዋናነት አስፈሪ ያደረጉት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
1. መነሻው በጣም የተለመደ የቶንሲል ህመም ሲሆን ይህም በብዙ ህፃናት ላይ የሚከሰት ችግር መሆኑ፣
2. የሚያደርሰው ተፅዕኖ በልብ የውስጠኛው ክፍል ላይ ስለሆነ እና ጉዳቱም የመደጋገም ሂደቱ የከፋ በመሆኑ በራሱ የመዳን ሂደት አለመኖሩ ብሎም ህይወትን አደጋ ላይ መጣሉ ናቸው።
የራሁማቲክ የልብ ህመም (Rheumatic heart disease) መነሻው በባክቴሪያ (Group A B hemolytic streptococcus) አማካኝነት ሲሆን የሚያጠቃውም በተለምዶ ቶንሲል (Bacterial Tonsilopharengitis) የሚባለውን ክፍል ነው።
ከዚህ በመነሳትም ተፈጥሮአዊ የበሽታ መከላከል ሂደትን በመጠቀም የተጋነነ ምላሽ (Autoimmunity by antigenic mimickery theory) በመስጠት ልዩ ልዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳትን ያስከትላል።
በዋናነት በትልልቅ የሰውነት መገጣጠሚያዎች (Migratorypolyarthirits to major joints) ላይ እብጠት ማምጣት ፣ የልብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረስ ፣ በቆዳና እና በነርቭ ህዋሳት ላይ (Subcutaneous nodules , erythema marginatum & Sydenham’s chorea) ምልክቶችን ያሳያል።
ከሁሉም ዓይነት ጉዳቶች ጠባሳ በዋናነት በትልልቅ የሰውነት መገጣጠሚያዎች(Migratorypolyarthritis to major joints) ላይ እብጠት ማምጣት ፣ የልብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረስ ፣ በቆዳ እና በነርቭ ህዋሳት ላይ ምልክቶችን ያሳያል።
ከሁሉም ዓይነት ጉዳቶች ጠባሳ በመተው ዘለቄታዊ ችግር የሚያስከትለው በልብ የውስጥ ክፍሎች ላይ (Carditis) የሚከሰተው ነው።
በልብ ክፍሎች በዋናነት ተፅዕኖ የሚያሳድረው ደም በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲሄድ እንዲሁም ለመዝጋት እና ለመክፈት የሚያገለግሉትን ቫልቭ የሚባሉ የልብ ክፍሎች ላይ (Primarily Mitral & Aortic valves) በመሆኑ በተገቢው መንገድ እንዳይሰራ (Stenosis or Regurgitation at the valves) ያደርጋል። ይህም የደም እንቅስቃሴን በማዛባት የልብ ስራ ላይ ከባድ ተፅዕኖ በማሳደር የልብ ድካም እንዲፈጠር እንዲሁም ሞት እንዲከሰት ያደርጋል።
ከላይ ለመረዳት እንደቻልነው በቀላሉ መከላከልና ማዳን ከሚቻለው የቶንሲል ህመም በመነሳት እንዲህ የከፋ ጉዳት እያስተናገድን እንገኛለን።
ለዚህ ማሳያ የሚሆን የእኛን ተሞክሮ እንግለፅላችሁ። በአንድ ወረዳ ላይ ባደረግነው የትምህርት ቤት ጥናት ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ጤናማ ህፃናት መካከል 4% የሆኑት ልባቸው ላይ ጉዳቱ ደርሶ (Rheumatic heart disease with mitral & aortic valve involvement) ሊገኝ ችሏል።
ከዚህ በመነሳትም ባደረግነው ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ የተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች ስልጠና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እና የብዙ ህፃናትን ህይወት መታደግ ችለናል።
በመሆኑም ችግሩን በመረዳት ፣ አሳሳቢነቱን ከግምት በማስገባት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ በመወጣት የቶንሲል ህመምን በአግባቡና በጊዜ እንዲታከም በማድረግ የሚሊዮኖችን የጠዋት ፀሀይ ወደ ፈካ ብርሀን የሚያሻግር ተግባር ላይ መሳተፍ ይገባናል።