የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ንዑስ ዘርፍ የሆነውን የአርትሮስኮፒ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ለታካሚዎች መስጠት ጀምሯል።

የአርትሮስኮፒ ህክምና በማንኛውም ሰው ላይ የመገጣጠሚያ ህመም በሚኖርበት ጊዜ ሰውነትን ሙሉ በሙሉ መክፈት ሳያስፈልግ በትንሽ ቀዳዳ ረቂቅ ካሜራዎች ወደ ውስጥ በማስገባት የተጎዳውን አካል ሙሉ በሙሉ በመመልከት የሚከናወን የቀዶ ህክምና አይነት ነው።

የአርትሮስኮፒ እና ጆይንት ሪፕለስመንት ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሀመድ ኢሳ የአርትሮስኮፒ ዘመናዊ ቀዶ ህክምና የተጎዳን የመገጣጠሚያ ክፍል በቀላሉ በካሜራ በመመልከት ህክምናውን በፍጥነት ለመስጠት ስለሚያስችል ታካሚዎች ረጅም ሰዓት ማደንዘዣ ላይ እንዳይቆዩ እና ህክምናው ከተጠናቀቀ በኋላ በቀላሉ አገግመው ወደ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም ህክምናው በሆስፒታሉ ውስጥ መሠጠት መጀመሩ ከዚህ ቀደም ይህን ህክምና ለማግኘት ወደ ውጪ ሀገር መሄድ ግዴታ የነበረውን ሁኔታ እንደሚያስቀር እና ህክምናውን ቀደም ብለው መስጠት በጀመሩ ሌሎች ሆስፒታሎች ላይ ያለውን ወረፋ የመጠበቅ ሂደት በተወሰነ መልኩ ለማሳጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በተጨማሪም በሆስፒታሉ ህክምናው እንዲጀመር የማሽን እርዳታ ላደረጉት ለ”አውስትራሊያን ዶክተርስ ፎር አፍሪካ” ድርጅት እና ለ”አድፋ” ድርጅት ሀላፊ ዶ/ር ግርሀም ፎርዋርድ እንዲሁም ለሆስፒታሉ አመራሮች ላቅ ያለ ምስጋናቸውን ለማቅረብ እንደሚወዱ ተናግረዋል።

Scroll to Top