የፆታዊ ጥቃት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመርቆ ተከፈተ

*****************************************************

አዲስ አበባ – የካቲት 11 – 2016 (ቅ.ጴ.ስ.ሆ)

የፆታዊ ጥቃት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በሆስፒታሉ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

ማዕከሉ በዓለም ላይ ብሎም በሀገራችን ኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል እና ጥቃት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተከፈ ነው።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሀም እሸቱ ማዕከሉ በኬዝ ማናጀር ደረጃ የተከፈተ እና የተለያዩ ባለሙያዎችን በማካተት በቀጣይ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ የተደራጀ በመሆኑ ከጥቃቱ አልፎ የህክምና አገልግሎት በማጣት በተጠቂዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት በማስቆም ረገድ ወሳኝ ሚና የሚኖረው እንደሆነ ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው ማዕከሉ የተገዶ መደፈር አደጋ ደርሶባቸው ለሚመጡ ተጎጂዎች ያልታሰበ እርግዝናና ሌሎች የአባላዘር ህመሞች እንዳይከሰቱባቸው የመከላከል ህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች፣ ህጻናት እና ወንዶች ልጆች የማኅበራዊ ፣ ስነ ልቦናዊ እንዲሁም የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ በሚገኝበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የፆታዊ ጥቃት ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ተጠቂዎች የተቀናጀ አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት እንዲችሉ ፤ ጥቃት አድራሾችም ሳይውል ሳያድር የሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ፓሊስና አቃቤ ህግ ተመድቦ አገልግሎት እንደሚሰጥ እንዲሁም ተጠቂዎች ሚስጢራዊነቱ በተጠበቀ ሁኔታ አገልግሎትና ፍትህ በማዕከሉ እንዲሚያገኙ የተናገሩት ደግሞ የሆስፒታሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲ/ር ተወዳጅ መርሻ ናቸው።

ዳይሬክተሯ አክለውም የሆስፒታሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ህጻናት እና ሴቶች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው ይህ ማዕከል ተከፍቶ ስራ እንዲጀምር ከዳይሬክቶሬቱ ጋር በመሆን ለሰሩ አካላትና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

_____________

“መኖራችን ለእርስዎ ነው!”

“OUR EXISTENCE IS FOR YOU!”

Scroll to Top